Walta Information Center  


በመቀሌ ከተማ የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ 42 ወጣቶች የኤችአይቪ ምርመራ አደረጉ

 

መቀሌ ጳጉሜን 5/1996/ዋኢማ/ የእንቁጣጣሽ በዓልን ምክንያት በማድረግ በመቀሌ ከተማ የሚገኙ 42 ወጣቶች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኤችአይቪ ምርመራ ማድረጋቸው ተገለፀ።

በኤድስ ማህበራዊ አገልግሎት ድርጅት /ኦሳ/ የመቀሌ  ኦሳ ቅርንጫፍ የኤችአይቪ ምርመራና ምክር አገልግሎት መስጫ ማዕከል ተገኝተው ምረመራውን ያካሄዱት የአዲሓቂ የፊልም ማህበር አባላት ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል እንደገለፁት፤ የሮም  ምርመራውን ያደረጉት በአዲሱ ዓመት እራሳቸውን አውቀው የባህርይ ለውጥ በማምጣት  ቀጣይ ህይወታቸውን ለማስተካከል በመወሰናቸው ነው፡፡

የማህበሩ አስተባባሪ ወጣት አማረ ታሪኩ በበኩሉ  ወጣቱ  በየጭፈራ ቤቱ በመገኘት ለልቅ የግብረ ስጋ ግንኙነት ከሚዳረግ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ተጠንቅቆ እንዲዝናና በማህበሩ አባላት በየሆቴሎቹና በየጭፈራ ቤቶች የኮንደም ዕደላ ማካሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም የሻማ ማብራት ስነ ስርዓት በማከናወን ህብረተሰቡ በመጪው ዓመት የአመለካከት ለውጥ በማምጣት እራሱን ከኤችአይቪ/ኤድስ እንዲከላከል የቅስቀሳ ስራ መደረጉን አስታውቋል።

በሌላ በኩል ኦፕሬሽን ሬስኩ ኢትዮጵያ የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሰባት ሺ ብር በመመደብ  ወላጆቻቸውን በኤድስ ያጡ ህፃናት የሚገኙባቸውን ከ200 በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎች በማሰባሰብ ከጳጉሜ 1 ጀምሮ የምሳ ግብዥ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጿል።

እንዲሁም ማህበር ህውነት ደቅ ሰብ የተባለ ድርጅት ከአንድ ባላሃብት ባገኘው የስምንት ሺ ብር እርዳታ ለ52 ወላጅ አልባ ህፃናት ለዓመቱ የሚያስፈልጋቸውን የትምህርት ቤት ዩኒፎርም፣ደብተርና የጽህፈት መሳሪያዎችን ማከፋፈሉን አስታውቋል።

የመቀሌ ዞን ወጣቶች ማህበር አባላትና የትግራይ ጦር አካል ጉዳተኞች ማህበር በበኩላቸው ዘጠኝ ሺ ብር በማዋጣት አቅም ለሌላቸው የማህበራቸው አባላት ልጆችና በኤች አይ ቪ ኤድስ ወላጆቻቸውን ላጡ ህፃናት የተለያዩ አልባሳትና የትምህርት ቁሳቁስ በማከፋፈል ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል::

 



© 1998 - 2002 Walta Information Center