Walta Information Center  


ለአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች ቋሚ ስያሜና አድራሻ ሊሰጥ ነው

 

አዲስ አበባ መስከም 1/1997/ዋኢማ/ ለአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች ቋሚ ስያሜና አድራሻ ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡

በአስተዳደሩ የመሠረተ ልማትና ግንባታ ሥራዎች ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ያለው ትናንት ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ መዲናና የልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ በመሆኗ መንገዶቿ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቀ ስያሜና አድራሻ እንዲኖራቸው ለማድረግ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡

የስያሜና የአድራሻ አሰጣጡ ከመንገዶች ጋር ተዛምዶ ስለሚዘጋጅና በየጊዜው የማይቀያየር መሆናኑ የአድራሻ ሥርዓቱን ቋሚ እንደሚያደርገው አቶ ተስፋዬ ገልፀው፤ በካርታ ላይ በቀላሉ ተነባቢ ስለሚሆኑም ማንኛውም ተጠቃሚ ወደፈለገበት ቦታ በቀላሉ እንዲደርስ ያስችላል ብለዋል፡፡

እንዲሁም ስያሜዎቹ በመንገዶቹ መነሻና መድረሻ ላይ ስለሚፃፉ ወደ ተፈለገበት ቦታ ለመድረስ በማስቻል ከአድራሻ ጋር የተያያዙ እንደ እሳት አደጋ፤ የወንጀል መከላከልና አምቡላንስ የመሳሰሉ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለመስጠት የላቀ ጠቀሜታ እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡

የመንገዶች ስያሜና የአድራሻ ሥርዓት የመዘርጋት ሥራ ካለፈው ዓመት ወዲህ መጀመሩን አቶ ተስፋዬ አስታውሰው፤ እስካሁን የጎዳና ስያሜና አድራሻ አሰጣጥ ሥርዓት ረቂቅ፤ የመንገድ ስያሜና አድራሻ ደንብ መዘጋጀታቸውንና አስፈላጊ የካርታና የሰነድ ዝግጅቶች መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡

የከተማዋን መንገዶች ለስያሜ በሚያመች መልኩ የመከፋፈል ሥራ ተጠናቆ ከዚህ ውስጥ 80 በመቶ ያህሉ ቁጥር ተሰጥቷቸው መመዝገባቸውን አመልክተዋል፡፡

ለመንገድ አሰያየሙ ሕብረተሰቡ በንቃት መሳተፍ እንዳለበት አቶ ተስፋዬ ገልፀው፤ በየክፍለ ከተማው ሥራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት በኩል ዕጪ ስያሜዎችን በመጠቆምና የተዘነጉ ነባር የመንገድ ስያሜዎችን በማስታወስ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እንዲሁም ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ሰዎችና ተቋማት ለአዲስ አበባ መሠረተ ልማትና ግንባታ ሥራዎች ባለሥልጣን ጽህፈት ቤት ዕጩ ስያሜዎቻቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡

የዕጩ ስያሜዎችን የማሰባሰብ ሥራ እስከ መስከረም 30 ቀን ለማጠናቀቅ መታቀዱን ጠቁመው፤ በአጠቃላይ ስያሜ የመስጠትና ምልክት የመትከል ሥራ በተያዘው በጀት ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ በአፍሪካ ህብረት አባል አገሮች የተሰየሙትን መንገዶች ጨምሮ ሦስት ሺ ለሚሆኑ መንገዶች ስያሜና አድራሻ እንደሚሰጥ ኃላፊው ገልፀዋል ዘግቧል፡፡

 



© 1998 - 2002 Walta Information Center